የSTEM ተማሪዎች የክረምት ትምህርት ፕሮግራም ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ተባለ፡፡
(ነሀሴ 22/2017 ዓ.ም ህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት)
መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንጅነሪንግ እና የሂሳብ (STEM) ትምህርት ማዕከልን አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ የሚታወስ ነው። ማዕከሉ የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ ከSTEM PAWOR ETHIOPIA ድርጅት ጋር በተፈጠረው ትስስር የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎችንም እንዲያገኝ ተደርጓል።
የSTEM ፕሮግራም ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የሚማሩትን በተግባር እያረጋገጡ የእውቀት፣የክህሎትና የፈጠራ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት፣ የክረምት እረፍት ጊዜያቸውን ለመደበኛው ትምህርት የሚያግዙ ጠቀሚ መፅሀፍትን በማንበብ ራሳቸውን የሚያዘጋጁበትና የወደፊት መዳረሻቸውን በጽሞና አስተውለው የሚወስኑበትን እድል የሚያመቻች ነው። በዚሁ መሰረትም ዩኒቨርሲቲው ከሀምሌ 7/2017 ጀምሮ በመስፈርት ተለይተው የተላኩለትን ከ9-12ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎችን ተቀብሎ በከፍተኛ ትምህርት መምህራን እያስተማረ ይገኛል።
ማዕከሉ በ2017 ዓ.ም የክረምት ወቅት በዩኒቨርሲቲው የድጋፍ ክልል ውስጥ ከሚገኙ 32 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 240 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ያደረገ ቢሆንም ወደ ዩኒቨርሲቲው የተላኩለት ተማሪዎች ግን 140 ብቻ መሆናቸውን የማህበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መምህር መሰረት አበበ ገልጸዋል። ጨምረውም ለዚህ ፕሮግራም መጠናከር የትምህርት ቤቶች፣ የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤቶች እና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ተናቦ መስራት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።




